/ሙላት

Published

- 3 min read

/እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ

img of /እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ

/የክርስቶስ የልደት በዓል ሁለት አስደናቂ ነገሮች የተፈጸሙበት ነው. የተጠበቀው ባልተጠበቀው መንገድ የመጣበት እና ያልተጠበቁት ባልተጠበቀ ቦታ የተገኙበት ነው. በኦሪትና በነቢያት ክርስቶስ ይመጣል የሚለውን ቃል የሰሙና ያነበቡ ብዙዎች ነበሩ. የጠበቁት ግን በነገሥታት ቤተ መንግሥትና በባዕለጸጎች እልፍኝ ውስጥ ነበር. የዓለምንና የሰው ልጅን ታሪክ የቀየረው ክርስቶስ በበረት ውስጥ ይወለዳል ብሎ የጠበቀ አልነበረም. በዚህም የተነሣ የዓለም ታሪክ በአስደናቂ ሁኔታ ሲቀየር ዓለም ራሷ ግን ተኝታ ነበር. 

/የዓለምንና የሀገርን ታሪክ የሚቀይሩ ነገሮች በተለመዱና በሚጠበቁ መንገዶች ላይመጡ ይችላሉ. ብዙዎች በሚያውቁትና በሚተነትኑት አካሄድም ላይከሠቱ ይችላሉ. እንዲህ ባለ ሁኔታ መረዳት የሚገኘው እኛ የማናውቀው, ያልደረስንበትና የማንገምተው ሌላም መንገድ ሊኖር እንደሚችል ለመቀበል ከተዘጋጀን ብቻ ነው. ነገሮች ሁሉ እኛ በምናውቀው, በምንገምተውና በለመድነው መንገድ ብቻ እንዲመጡ ከጠበቅን ሊያልፉን ይችላሉ. የቤተ ልሔም ከተማና የይሁዳ አውራጃ ሰዎች የዓለምን ታሪክ ከቀየረው ከክርስቶስ ልደት ሳይሳተፉ የቀሩት ከለመዱትና ከሚያውቁት ውጭ ለሚመጣ ነገር ዝግጁዎች ስላልነበሩ ነው.

/የቤተልሔም ከተማና የይሁዳ አውራጃ ሰዎች በለመዱትና በሚያውቁት መንገድ የሚመጣን ነገር ሲጠብቁ, ባልለመዱትና በማያውቁት መንገድ የሚመጣን መፍትሔ ለመቀበል ዝግጁ የሆኑ ሌሎች  አካላት ቤተልሔም ደርሰው ነበር. እረኞችና ሰብአ ሰገል. ሌሊቱን ሙሉ መንጋቸውን ሲጠብቁ ያደሩት የቤተልሔም እረኞች በአካባቢያቸው የነበሩትን መላእክት ለመመልከት ዕድል አግኝተዋል. ጊዜው ምሽት ነው. ምሽት ደግሞ የዕንቅልፍ ጊዜ ነው. ለሕዝብ ቆጠራ ወደ ቤተልሔም የመጡ ሰዎች ከተማዋን አጨናንቀዋታል. ከዚህ ያለፈ እንግዳ ነገር የጠበቀ የቤተልሔም ሰው የለም. ሁሉም የተለመደን ነገር በተለመደ መንገድ በማከናወን ተኝቷል.

@AbiyAhmedAli posted on TwitterX

/እረኞቹ ግን ከተኛው ማኅበረሰብ ተለይተው በሜዳ ላይ በንቃት ነበሩ. ይሄ ብቻ አይደለም. የዓለምን ታሪክ የቀየረው ክርስቶስ በእንግዶች ማደሪያ ሥፍራ ስላላገኘ የመጣው ወደ በረት ነው. የከተማው ሰዎች ሊያደርጉ ያልደፈሩትን እረኞቹ በረታቸውን ለዮሴፍና ለድንግል ማርያም ለቅቀው ወደ ሜዳ ወጡ. እረኞቹ ከሕዝቡ የተለየ መንገድና የተለየ ዝግጁነት ነበራቸው. በዚህ የተነሣ ከሊቃውንቱ, ከፈሪሳውያኑና ከሰዱቃውያኑ ተለይተው ያልታሰበውን ታሪክ ያልታሰቡት እረኞች ለማየት በቁ.

/የቤተልሔምን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ንጉሥ ሄሮድስንም ባስደነገጠ መንገድ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ‹የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው› እያሉ ከእረኞቹ ቀጥለው መጡ። ማንም አልጠበቀም. ያልተጠበቁት ሰብአ ሰገል ባልተጠበቀ ቦታ በበረት ተገኙ. ካልተለመደ ሥፍራ, ባልተለመደ መንገድ ተጉዘው, ያልተጠበቀ ቦታ ተገኙና ያልጠበቁትን ተአምር አዩ. 

/ሀገርን ምንጊዜም የሰው ልጅ ሲጓዝባቸው በኖሩ መንገዶች ብቻ መታደግ አይቻልም. ሰው ሁሉ በሚያውቃቸው, በለመዳቸውና በተረዳባቸው መፍትሔዎች ብቻ ሀገርን መመንጠቅ አይቻልም. መኪኖችና አውሮፕላኖች በሚጓዙበት መንገድ መንኮራኩሮችን ወደ ሕዋ መውሰድ እንደማይቻለው ሁሉ. ወደ ሕዋ ለመሄድ የምድር ስበትን ሰብሮ, በፍጥነትና በኃይል ባልተለመደ የጉዞ ስልት መመንጠቅን ይጠይቃል. 

/እንዲህ ያለ ጉዞ ከተለመደውና ከሚታሰበው መንገድ ወጥቶ መሄድን የግድ ይላል.  ስለዚህም ይሄንን መንገድ የሚረዳ ከሚጠበቀውና ከሚታሰበው ውጭ ለመጓዝ ፈቃደኛ የሆነ ወገንን ይፈልጋል. አሁን ሀገራችን ያለችው እንዲህ ባለ ጉዞ ላይ ነው. 

/በተለመደ እሽክርክሪት ነባር ችግሮችን ፈትቶ አዲስ ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም. የተለየ, ያልተጠበቀ, ከምናውቀው የወጣና ያልታሰበ መንገድ ይፈልጋል. በርግጥ እንዲህ ያለው መፍትሔ በተለመደው መንገድ ለሚያስቡና ለሚጓዙ እንግዳና የሚረብሽ እንደሚሆን እሙን ነው. 

/ለመቀበልና ለማመንም ይከብዳቸዋል. እንደ እረኞች ዝግጁ እንደ ሰብአ ሰገል አሰላሳይ የሆኑ ወገኖች ግን ‹የት ነው› እያሉ ፈልገው ይደርሱበታል. በተለመደው መንገድ የተለመደውን የሚከውኑ ወገኖች ቢገርማቸውም፤ ባልተለመደው መንገድ የሚመጣው እንግዳው መፍትሔ ግን, ታሪክን ላይመለስ መቀየሩ አይቀሬ ነገር ነው. መጀመሪያ የሚቀበሉት ጥቂቶች ቢሆኑም እየቆዩ ግን ብዙዎች እየተረዱትና እየተቀበሉት መሄዳቸው ርግጥ ነው. 

/የክርስቶስን ልደት ስናከብር በልደቱ ካገኘነው በረከትና መዳን ቀጥለን ዓለም የተቀየረበትን መንገድ ማጤንና እኛም የምንሄድበትን መንገድ መገምገም አለብን. ሁሉም ነገር ለምክርና ለተግሣጽ እንዲሆነን ተጽፏልና.

/በድጋሜ መልካም የልደት በዓል ይሁን.    

/ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

/ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

/ታህሳስ 27, 2016 ዓ.ም